ማለፊያ (ፉአድ ሙና) ክፍል ሰባት *** ሲሀም ደፋሯ … ትዕግስት አጣች፡፡ ካላገባች ቂያማ የሚቆም አስመሰለችው፡፡ አሁን ገና በሀያዎቹ መጀመሪያ ላለች ታዳጊ ትዳር የሞት መድሀኒት ነው የተባለ ያህል እንዲህ መክለፍለፍ ምንድነው? ወይ አስረግዟት ይሆናል ነውሯን ለመሸፈን ነው እንጂ እንዲሁ ለማግባት ብቻ ብላ አይሆንም፡፡ የሚያውቋት ሁሉ የሚሰጡት መላ ምት ነው፡፡ በእርግጥ አብደላህ የሲሀምን ህግ የነካው ያገባት ምሽት ላይ ነው፡፡ ያጣደፋት እርግዝናም አልነበረም፡፡ ምናልባት ገና እንደሆነች … እሷ እንደምትለውም ህይወት እንደማያመልጣት ማሰብ አልቻለችም፡፡ ለዚህ ደግሞ የአብደላህ ስብከት ጥሩ አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡ ካገባች ሶስተኛ ቀን ተቆጥሯል፡፡ ከመጀመሪያው ቀን በኋላ ወዲያው ወደ ቤታቸው ገብተዋል፡፡ ዶርም ማደር የሚባለው ነገር እግር እግር ብሏታል፡፡ ከዚህ በኋላ ዶርም ላለማደር ወስናለች፡፡ የራሷ ቤተ-መንግስት ላላት ሴት ዶርም ምንድነው? ለሴት ልጅ ቤቷ ቤተ-መንግስቷም አይደል? ባሏ እሱ ወጣ ብሎ እስኪመለስ ንባቧ ላይ እንድታተኩር እያበረታታት … ከባሏ ጋር ያለመችውን አይነት ጊዜ እያሳለፈች ነው፡፡ በውሳኔዋ እጅጉን ተደስታለች፡፡ ፍርሀቷ ሁሉ እንኳን አደረግኩት በሚል ስሜት ተተክቷል፡፡ ዛሬ ባሏ በጠዋት ስራ ብሎ ሄዷል፡፡ ዛሬ አብረው እንዲያሳልፉ ብትለምነውም ከትምህርትሽ ትሳነፊያለሽ ብሎ በራሷ አመካኝቷል፡፡ አንብባ ደከም ሲላት እስከዛሬ ያልደወለችላቸው ቤተሰቦቿ ጋር ለመደወል አሰበች፡፡ ጓደኞቿ ጋር ደዋውላለች … የቀራት ቤተሰቦቿን መጋፈጥ ነው፡፡ በእርግጥ ምህረትና ቤቲ በልጅነቷ እንደተቀጨች ተሰምቷቸዋል፡፡ ገና ላይፍን ሳታጣጥም ወይም በአማርኛ ሲብራራ ሳትሸረሙጥ፣ ከወንድ ወንድ እየዘለለች ሳታድር፣ በየክለቡ እየዞረች ሳትጨብስ፣ ገላዋን ለቡዳ ሳታስጎበኝ፣ ወንድ ሳታደባድብበት ማግባቷ በእነሱ የሸርሙጦሎጂ እውቀት መሰረት በአጭሩ መቀጨት ነው፡፡ ከብዙ ፈራ ተባ በኋላ በየቀኑ ሲቀጠቅጥ ወደነበረው ወንድሟ ደወለች፡፡ ‹‹ሲሁ …›› ‹‹ጀም …›› ‹‹ምን ሆነሽ ነው በአላህ?›› ‹‹ምኑን?›› ‹‹እሺ አገባሽ … ታዲያ ቤተሰብ ይቆረጣል እንዴ?›› ‹‹ምታናግረኝ አልመሰለኝም! … ለመቆጣት የደወልክ መስሎኝ ነው፡፡›› አለቀሰች፡፡ ‹‹ባይሆን ደስ ይለኝ ነበር … ሁላችንም ደስ ብሎን … እኔ እንዳገባሁት ተደግሶ ዘመድ አዝማድ ተሰብስቦ … ባባና ማማም ተደስተው ቢሆን ደስ ይለኝ ነበር … ግን ከሆነ በኋላ ምን ይደረጋል?›› ‹‹እኔም እንደሱ በክብር ባገባ ምኞቴ ነበር፡፡ ባባ እንቢ አለ፡፡ ቤተሰብ እንደሌለው ሰው ለብቻዬ አገባሁ፡፡›› ተንሰቀሰቀች፡፡ ‹‹አይዞሽ በቃ … እኔማ መልስ ልጠራሽ ነበር የደወልኩት!›› ‹‹ወላሂ?›› ‹‹አዎ መች ይሻላል? ባልሽም የሚመቸውን ቀን መርጠን እራት እኛ ቤት እንድንበላ አስበን ነው፡፡›› ‹‹አባ መልስ እንደጠራኸኝ ከሰማ ምንም አይልህም?›› ‹‹ይገለኛል እንጂ ጭራሽ! ማንም ሳይሰማ እንድናደርገው ነው ያሰብኩት!›› ሲሀም ከጎኗ ሰው እንዳላት ተሰማት፡፡ በወንድሟ እንደዚህ ተደስታ አታውቅም፡፡ እውነት ለመናገር ግን መጀመሪያ ማግባቷን ሲሰማ እንደ እብድ አድርጎት ነበር፡፡ እንዲህ የለዘበው ሚስቱ አረጋግታውና ብዙ መክራው ነው፡፡ ‹‹ሰው እንደሌላት ከተሰማው ባሏም ይንቃታል፡፡›› የሚለው የሚስቱ ንግግር ቢያንስ በባሏ እንዳትናቅ ማቅረቡ ይሻላል ብሎ እንዲወስን አደረገው፡፡ ‹‹እወድሀለሁ፡፡›› እንደ ህፃን ተንሰቀሰቀች፡፡ ባሏ ሲመጣ እንደ ህፃን ልጅ እየተፍለቀለቀች ወንድሟ ያላትን ነገረችው፡፡ ‹‹ተይ ግን ይኼ ነገር ወጥመድ እንዳይሆን!›› ‹‹የምን ወጥመድ?›› ‹‹ይዘውሽ ቤት ምናምን ሊቆልፉብሽ ቢሆንስ?›› ‹‹ከዚህ በኋላ በጭራሽ … ደግሞ ወንድሜን አውቀዋለሁ የሴራ ሰው አይደለም፡፡›› ‹‹ለክፉም ለደጉም … ጓደኞቼን ይዤ እንሄዳለን፡፡›› ‹‹እንደሱም ማድረግ ይቻላል፡፡›› ትልቅ ሸክም የወረደላት መሰላት፡፡ ሌላው ቢቀር ዘመዴ ብላ የምትሄድበት ቦታ መኖሩ አረጋጋት፡፡ ቀናት ገፍተው የመልሱ ቀን ደረሰ፡፡ አብደላህ ጓደኞቹን ሰብስቦ ወደ ወንድሟ ቤት አመሩ፡፡ በእርግጥ ልቡ በጣም ፈርቷል፡፡ ወንድሟን ከዚህ ቀደም ያገኘው ቀን ያደረገለት አቀባበል እንዲፈራውና መጥፎ መጥፎውን እንዲያስብ አድርጎታል፡፡ በር ላይ ሲደርሱ ጀማል ወጥቶ ተቀበላቸው፡፡ እህቱን ሲያያት ሆድ ባሰው! አይኖቹን ከመርጠብ ታገላቸው፡፡ ዓመታት የናፈቀውን ሰው እንዳገኘ ጎትቶ ደረቱ ላይ ለጠፋት፡፡ ሲረጋጋ ወንዶቹን በየተራ ሰላም ማለት ጀመረ፡፡ ሁኔታውን ሲመለከት አብደላህ ተረጋጋ፡፡ ጀማል ከዚህ ቀደም ያገኘው ሰው አልመስል አለው፡፡ በጣም ተጫዋችና ቀለል ያለ ሰው ሆነበት፡፡ ለመልሱ የተዘጋጀው ምግብ መለስተኛ ሰርግ ይመስላል፡፡ ጀማል ሰው መጥራት ስለማይችል እንጂ ቢደግስና ሰው እንዳላት ቢያሳይ ደስ ባለው ነበር፡፡ ‹‹እና እንዴት ነው ሙሽርነት?›› ከሪማ እየተፍለቀለቀች ጠየቀቻቸው፡፡ ‹‹ቆንጆ ነው፡፡›› ሲሀም ተሸኮረመመች፡፡ አብደላህ በጀማል ማንነት በጣም ተደንቋል፡፡ እንዲህ ፈታ ያለ ሰው ይሆናል ብሎ አልገመተም፡፡ በልተው ሲጨርሱ አብደላህ ከመቀመጫው ተነስቶ ቆመ፡፡ ‹‹ኧረ ገና ነው ሰዓት …›› ‹‹አይ ለመሄድ አይደለም … ስጦታ ነበረን፡፡›› ጓደኞቹ ያመጡትን ስጦታ ማውጣት ጀመሩ፡፡ በባህሉ መሰረት ለአባቷና እናቷ ስጦታ መስጠት ስላልቻሉ ወንድሟና ሚስቱን አለበሱ፡፡ ጀማልና ከሪማም ያልጠበቁት ስለነበር ክብር ተሰማቸው፡፡ ተደሰቱ፡፡ እንግዶቻቸውን ከሸኙ በኋላ አልጋቸው ላይ አረፍ ብለው ማውጋት ጀመሩ፡፡ ‹‹አንተ ጥሩ ልጅ ይመስላል ባሏ!›› ‹‹አዎ ብዙም አይከብድም!›› ‹‹አንተ ደግሞ በቃ ምንም አያስደስትህማ!›› ‹‹አይ ደስ ብሎኛል … እንዲህ አጋኖ መግለፅ ስለማይገራልኝ ነውኮ!›› ‹‹መርዙን የእሱ ሳህን ላይ በደንብ አድርጌያለሁ፡፡›› ‹‹ምን?›› ‹‹መርዙን ነዋ በደንብ አድርጊበት አላልከኝም?›› ‹‹መች ነው ያልኩት?›› ‹‹ቢሞት አሪፍ አይደል እንዴ!›› ‹‹ለምንድነው የሚሞተው? የእህቴ ባል እኮ ነው!›› ‹‹ያው በግድ ነዋ የወሰዳት! መች ፈቅደህ ሰጠኸው?›› ‹‹እየቀለድሽ ነው አይደል?›› ‹‹የምን ቀልድ ነው? እኔ ደስ የሚልህ መስሎኝ ነው ያደረግኩት!›› ‹‹ግድያ?›› ‹‹ሀሀሀሀሀ … አየሀ ትወደዋለህ አላልኩህም?›› ‹‹ማንን?›› ‹‹ባሏን ነዋ! የእህትህ ባል ነው ከዚህ በኋላ!›› ‹‹እና እየቀለድሽ ነዋ!›› ‹‹ምኔ ነው ነብሰ ገዳይ የሚመስልህ … ኧረ ቀልዴን ነው፡፡›› ‹‹እኮ! እንኳንም ጠራናቸው ባይሆን አሪፍ ሀሳብ ነው ያመጣሽው! እህቴ እንዲህ ስትፍለቀለቅ ካየሁ ቆየሁ!›› ደስ ብሏቸው ወደ እንቅልፋቸው ሰጠሙ፡፡ *** ‹‹ሲጀመር በጣም ቆንጆ ስራ ነው ይኼ!›› ‹‹አንተ እኛን መቃረን ስለምትወድ ነው እንጂ ማርገዝ የሚባል ነገር አለ እኮ!›› ‹‹ለማርገዙ የወሊድ መቆጣጠሪያውስ?›› ‹‹እሱ መች ይቻላል በናንተ ሃይማኖት?›› ሲሀም ምልልሳቸውን ታደምጣለች፡፡ አስተማሪ ወጥቶ ከክላስ ከመውጣታቸው በፊት ቁጭ ብለው እያወጉ ነው፡፡
https://t.me/fuadmu/3942